Pages

Thursday, October 23, 2014

ለመሆን ሣይሆን እንዴት ይሆናል ቢሆን

የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የሴት ጦማሪያንን አቤቱታ አስተባበለ
በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ ከተመሠረተባቸው ጋዜጠኞችና ጦማሪያን መካከል፣ ሴት ጦማሪያን ማኅሌት ፋንታሁንና ኤዶም ካሣዬ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እየደረሰባቸው ያለውን በደል በሚመለከት ለፍርድ ቤት ያቀረቡትን አቤቱታ፣ ማረሚያ ቤቱ ጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. አስተባበለ፡፡
የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት አስተዳደርን ወክለው ፍርድ ቤት የቀረቡትና በማረሚያ ቤቱ የሴት ታራሚዎች መምርያ ኃላፊ ሱፐር ኢንቴንደንት አየለች አሰፋ ለፍርድ ቤቱ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ቀጠሮ ማረሚያ ቤቱ ጦማሪያኑ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ቀርቦ እንዲያስረዳ ታዞ ለምን እንዳልቀረበ ተጠይቀው፣ ‹‹የደረሰን ነገር የለም፣ ሁለተኛው ትዕዛዝ ስለደረሰን መጥቻለሁ፤›› ካሉ በኋላ፣ ጦማሪያኑ እንደ ማንኛውም ታራሚ በአግባቡ እንደተያዙ በማስረዳት የጦማሪያኑን አቤቱታ አስተባብለዋል፡፡
የጦማሪያኑ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ያለፈው ነገር አልፏል ቢባል እንኳን መብታቸው ወደፊት ሊከበርላቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ እንደ ማንኛውም ታራሚ በማረሚያ ቤቱ ደንብ መሠረት ለመስተናገድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡
‹‹አሸባሪዎች›› ተብለው ከማንኛውም እስረኛ ጋር እንደማይገናኙና ብዙ ጠያቂዎቻቸው ‹‹ስማችሁ አልተመዘገበም›› ተብለው ሳይጠይቋቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውም ቢሆኑ ከ6፡10 ሰዓት እስከ 6፡20 ሰዓት ብቻ ለአሥር ደቂቃ እንደሚያነጋግሯቸው በማስረዳት፣ በቀጣይ እንዲስተካከልላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ እንደ ማንኛውም የማረሚያ ቤት ታራሚ እንዲያዙ፣ ከዚህ በኋላ ሌላ አቤቱታ የሚቀርብ ከሆነ ፍርድ ቤቱ በሚቀርብለት አቤቱታ መሠረት ማጣሪያ አድርጐ ተገቢ ዕርምጃ እንደሚወስድ ተወካይዋን አስጠንቅቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በዕለቱ የተያዘው ቀጠሮ የሴት ጦማሪዎቹ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ምላሽ እንዲሰጥ መሆኑን በማስታወስ፣ እነሱም ችግር አለ የሚሉ ከሆነ አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችሉ በማስታወቅ፣ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
http://www.diretube.com/articles/read-addis-ababa-prisons-administration-denied-abuses-on-jailed-female-bloggers_7022.html#.VEkH2Ffzm_Ihttp://www.diretube.com/articles/read-addis-ababa-prisons-administration-denied-abuses-on-jailed-female-bloggers_7022.html#.VEkH2Ffzm_I

No comments:

Post a Comment