
የወያኔ ባለስልጣኖችና በየአካባቢዉ የኮለኮሏቸዉ ምስለኔዎች አካባቢዉን በግድ እንዲለቅ የተደረገ ህግ አክባሪ ዜጋ የለም፤ የተባረሩት ህግ የጣሱ ግለሰቦች ብቻ ናቸው፣ በማለት አሳፋሪ ድርጊታቸዉን ለመደበቅ ሲሞክሩ ታይተዋል። ሆኖም ከጉራ ፈርዳና ከአካባቢዉ ተፈናቅለዉ ወደ መጣችሁበት አካባቢ ተመለሱ ተብለው በየሜዳው ያለምግብ፣ ውኃና፤መጠለያ የተበተኑ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ለወገኖቻቸውና ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ የድረሱልን ጩኸት ሲያሰሙ መሰንበታቸዉ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነዉ። ወያኔ በዚህ በያዝነዉ አመት ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ በአማራዉ ህዝብ ላይ አዲስና ሰፋ ያለ የጥቃት ዘመቻ ጀምሯል። በደቡቡ የአገራችን ክልል በጉራፈርዳ የጀመረዉን አማራውን ነጥሎ የማጥቃትና የማንገላታት ዘመቻ አሁን ደግሞ በሰሜን ምስራቅ የአገራችን ክፍል በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቀጥሏል። ሰሞኑን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ለረጂም አመታት ከአካባቢዉ ህብረተሰብ ጋር ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩ አያሌ የአማራ ተወላጆች ያፈሩትን ንብረት ለመሰብሰብ እንኳን ግዜ ሳይሰጣቸዉ የኔ ብለው ከሚጠሩት የመኖሪያ ቦታቸዉ እንደባዳ እየተገፉ እንዲወጡ ተደርገዋል። እዚህ ላይ አንድ እጅግ የሚያሳዝን ነገር ቢኖር በገዢዉ ፓርቲ ኢህአዴግ ዉስጥ አማራን እወክላለሁ ባዩ ብአዴን ወያኔ በአማራዉ ህዝብ ላይ የሚያደርሰውን በደል ዝም ብሎ መመልከቱ ብቻ ሳይሆን ባለፈው አመት ከጉራ ፈርዳ ዘንድሮ ደግሞ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ እየተባረሩ እየወጡ ባሉ አማራዎች ላይ እየተፈጸመ ባለው ወንጀል ላይ ተባባሪ መሆኑን አሳይቷል። ግንቦት ሰባት የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔ በአማራዉ ህዝብ ላይ ያደረሰውንና በማድረስ ላይ ያለውን ይህ ነዉ የማይባል ግፍና መከራ ከዚህ ቀደም እንዳደረገዉ ሁሉ አሁንም አጥብቆ ያወግዛል። ከዚህ በተጨማሪ ወያኔ በዚህ በኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት የትግል ምእራፍ ውስጥ በደም የተቀባ፣ የቀለመ አኩሪ ታሪክ ያለውን የአማራውን ህዝብ መልሶ መላልሶ የሚያጠቃውና ይህንን ታላቅ ህዝብ ከየቦታዉ የሚያፈናቅለው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ከአማራዉ ህዝብ ጋር ብቻ በማያያዝ አገራችንን ለማዳከምና አንዱ ኢትዮጵያዊ በሌላዉ ኢትዮጵያዊ ላይ የሚደርሰዉን ግፍና መከራ “ምን አገባኝ” ብሎ እንዲመለከት ለማድረግ ባለው እጅግ አደገኛ ዕቅድ መሠረት መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲገነዘብ በጥብቅ ያሳስባል። ከዚህም በተጨማሪ በአማራው ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ባለው እጅግ አስከፊ ወንጀል በግልም ሆነ በቡድን፣ የንጹሀንን ደም እያፈሰሳችሁ ያላችሁ ወንጀለኞችና ተባባሪዎች፣ ከያላችሁበት ታድናችሁ ለፍርድ እንድትቀርቡ ንቅናቂያችን የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት በግልጽ እንድታውቁት ይገባል። በአማራው የደረሰው ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ዜጎች ጥቃት ነው እንላለን። ግንቦት ሰባት ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በግለሰብ ደረጃ የምንደሰትበትን ነጻነት የምናስጠብቀው በህብረት ነውና ወያኔ በአሁኑ ግዜ በአማራው ወገናችን ላይ የሚያደርሰውን ግፍ፤ መከራና መፈናቀል በእያንዳንዳችን ላይ እንደደረሰ በመቁጠር ይህንን ግፍ በመፈጸም የማይሰለቸውን ዘረኛ አገዛዝ በተባበረ ህዝባዊ ትግል ከአገራችን ለማስወገድ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ትግል ጥሪ ያስተላልፋል። ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ መጋቢት 2005 ዓ. ም
No comments:
Post a Comment