እኔ የምላችሁ… ኢህአዴግ በቅርቡ በባህርዳር ለሚያካሂደው 9ኛው ጉባኤ 15 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከውጭ አገራት እንደጋበዘ ሰማችሁ አይደል? (የአገር ቤት ፓርቲን ትቶ ከውጭ “መቀላወጥ” ምን ይሉታል?) በጣም እኮ ነው የሚገርመው ---- ኢህአዴግ ከአገር ውስጥ አንድ ፓርቲ እንኳን ሳይጋብዝ አስራምናምን ከውጭ? (የፓርቲ ጉባኤ ድንኳን ሰበራ እንዳይጀመር ሰጋሁ!) ቆይ ግን--- ይሄ ጉደኛ ፓርቲ እነዚህን ሁሉ የፓርቲ ባልንጀራዎች መቼ ነው የተዋወቃቸው? እዚህ ከአንድ ተቃዋሚ ጋር በተጣላ ቁጥር ውጭ ካለ አንድ ፓርቲ ጋር ባልንጀርነት ሲመሰርት ነበር ማለት ነው? የኢህአዴግ ቃል አቀባይ አቶ ሴኮ ቱሬ (የስማቸውን ፍቺ ባውቀው ደስ ይለኝ ነበር) ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ የኢህአዴግ ዘጠነኛ ጉባኤ ፓን አፍሪካኒዝምን ያንፀባርቃል ብለዋል፡፡
(በአገር ውስጥ ባለው የፓርቲዎች ግንኙነት አኩሪ ታሪክ ባይኖረውም ማለት ነው!) አንድ ነገር ግን መዘንጋት የለበትም፡፡ ምን መሰላችሁ--- ለሌሎች ሃሳባችንንና መስመራችንን ስናጋራ ልዩ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ሁሉ ነገራችንን ዘርግፈን መስጠት የለብንም፡፡ ለምን መሰላችሁ --- አንዳንዴ እንጠቅማለን ብለን ልንጎዳ እንችላለን፡፡ አያችሁ ---ኢህአዴግ ለአፍሪካውያን የሚያጋራው በጎ በጎ ነገሮች እንዳሉት ቢናገርምሁሉ ፈጽሞ ማጋራት የሌለበት አሉታዊ ነገሮችም እንዳሉት ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት!! እስቲ አስቡት…የፓርቲውን የ“ምስጢራዊነት” ባህል ለሌሎች አፍሪካውያን ቢያጋራ ምን ዓይነት ችግር ላይ እንደሚወድቁ! (ለራሱም እኮ አልጠቀመውም) “እኔ ብቻ ነኝ የአገር መድሃኒት” የሚለውንም ጎጂ ባህሉን ለአፍሪካ ወንድሞች ማጋራት የለበትም (ትርፉ ዕዳ ነዋ!) የፍረጃ ልምዱንም (ኪራይ ሰብሳቢ፣ የሻቢያ ተላላኪዎች፣ ጥገኞች…ወዘተ) አጋራለሁ ብሎ እንዳያስብ እንመክረዋለን (እንዴ ማፈሪያ ይሆናላ!) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢህአዴግን ሲበዛ ባተሌ መሆን ለአንድ ሁነኛ ባልንጀራዬ ሳወያየው ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ… “ኢህአዴግ የተባለ ሁሉ (አመራር፣ ካድሬ፣ አባል ወዘተ…) ከምርጫው በኋላ ቫኬሽን ይወጣል” “ኧረ ይገባቸዋል…ግን ለምን ያህል ጊዜ ነው?” ጠየቅሁት፡፡ “እስከቀጣዩ ምርጫ!” “እስከ ቀጣዩ ምርጫ? እስከ 2007 ማለትህ ነው?” “አግኝተኸኛል … ያኔ ምርጫ ሲቃረብ ደግሞ ስብሰባ፣ ውይይት፣ ብሶት መስማት … የኮንዶሚኒየም እጣ ማውጣት፣ የልማት ዲስኩር … መቀወጥ ይጀምራሉ … ምርጫው ሲጠናቀቅ እንደገና ቫኬሽን …” “ቆይ እነሱ ቫኬሽን ሲወጡ ማነው የሚመራው … ማለቴ … የሚያስተዳድረው?” “እነሱው! ካሉበት ሆነው በሞባይል ያስተዳድሩናል … በሞባይል ያዛሉ … በሞባይል ቅሬታ ይሰማሉ … በሞባይል ደንብና መመሪያ ያወጣሉ … ቀላል ነው … ለምደውታል” “ምኑን?” “ቫኬሽን ላይ ሆኖ አገር መምራቱን!” ትንሽ ቆዘምኩ፡፡
No comments:
Post a Comment